የፈረንሳዩ ዴላሞት ኢንተርፕራይዝ ምግብ ማቀነባበሪያ ኩባንያ በኢትዮጵያ የደረቅ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር)፤ የኩባንያው ባለቤቶች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በስንዴ ምርት ሀገራዊ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ በተጀመረበት ወቅት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የተፈጠረው የስንዴ ምርት አቅርቦት መስተጓጎል ተጽእኖ እንዳያሳርፍባት በመንግስት በተወሰደው ርምጃ ከውጪ ስንዴ ለማስገባት ይወጣ የነበረው ከ750 ሚሊየን ዶላር በላይ በሀገር ውስጥ መተካት መቻሏን ጠቅሰው፤ በስንዴ አምራችነት ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰዋል።
ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለመስራት ላሰበው ጣፋጭና ደረቅ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በዋናነት ከሚያስፈልጉ ግብአቶች ውስጥ ስንዴ፣ የቅባት እህሎች እና የእንስሳት ተዋጽኦ መሆናቸውን የኩባንያው መስራች ሴባስቲያን ዴላሞት አብራርተዋል።
ኩባንያው ለሚያመርተው ምርት ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን ከኢትዮጵያ እንደሚጠቀም ገልጸው፤ በዘርፉ ያካበተውን ቴክኒካል ዕውቀት ለኢትዮጵያ ባለሙያዎች በማስተለለፍ ለሀገራዊ ክህሎትና እውቀት መዳበር ሚናውን መጫወት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
በመሆኑም ኩባንያው በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ፋብሪካ በመክፈት በምግብ ማቀነባበር ሥራ የመጀመር ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ