የውጭ አገር ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እየተከናወነ ያለው ስራ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የተሻለ እድል እንደሚፈጥር የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ብርሃኑ ዓለሙ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት የአሰራር ማዕቀፎችን ጨምሮ የውጭ ባንኮች በባንክ ዘርፉ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮች ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የአሰራርና የሰው ኃይል አቅማቸውን፣ የቴክኖሎጂ አቅማቸውንና ተደራሽነታቸውን ይበልጥ በማጎልበት የተወዳዳሪነት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ዶክተር ብርሃኑ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ተከልክለው የነበሩ ዘርፎች ክፍት መደረግ ጀምረዋል።
በ10 ዓመት የልማት እቅድ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ማሳደግና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል።
መንግስት በፖሊሲ ማሻሻያው የውጭ አገር ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀዱ በባንኮች መካከል ያለውን ተወዳዳሪነት የማሳደግና የክፍያ ስርዓትን ጨምሮ የአገልግሎት አሰጣጥን ያቀላጥፋል ብለዋል።
እንዲሁም የሰው ኃይል አቅምና የቴክኖሎጂ አሰራርን ለማጎልበት እንዲሁም የካፒታል ፍሰትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው ዶክተር ዓለሙ የገለጹት።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ወሳኝ አበርክቶ አለው ያሉት ባለሙያው ይህም የውጪ ንግድን ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ከሚመጡት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ራሳቸውን በቴክኖሎጂና አገልግሎት አሰጣጥ ማብቃት እንዳለባቸው ባለሙያው መክረዋል።
መንግስትም ለአገር ውስጥ ባንኮች ድጋፍ መስጠትና ከውጭ የሚመጡ ባንኮች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበትም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ የፌደራል መንግስት፤ ከአገር ውስጥ ገቢ ከ15 በመቶ የበለጠ ገንዘብ በብድር ማግኘት እንዳይችል ገደብ ይጥላል።
ዶክተር ብርሃኑ እንዳሉት ከዚህ በፊት መንግስት ላይ የተቀመጠ የብድር ጣሪያ አለመኖሩ ገንዘብ በብዛት ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ በማድረግ የብር መግዛት አቅም እንዲዳከምና የዋጋ ንረት እንዲፈጠር መንስኤ ነበር ይላሉ።
መንግስት መበደር በሚችለው የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ መጣሉ የ ‘ሞኒተሪና’ እና ‘ፊስካል’ ፖሊሲዎች ውጤታማ ለማድረግና የብሔራዊ ባንክን ተቋማዊ አቅም ለመገንባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ገደቡ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና መንግስት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን የአገር ውስጥ ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ እንደሚያስችለው ገልጸዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 35ኛ መደበኛ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ስለ ባንክ ስራ የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን ታክለውበት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ መወሰኑ ይታወቃል።
ምንጭ፦ ኢዜአ