ኮንሴፕቶስ የተሰኘ የኮሎምቢያ ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በኢንቨስትመንት በመሰማራት ካገለገሉ የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶች ለኮንስትራክሽን የሚሆኑ ግብዓቶችን የማምረት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የኩባንያውን ከፍተኛ አመራሮች በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የኩባንያው አመራሮች ስለ ኢንቨስትመንት ፍላጎታቸው ዝርዝር ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን፥ በቀረቡ የቅድመ ኢንቨስትመንት ሃሳቦች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ አክሊሉ፥ ኩባንያው ያቀረበው የኢንቨስትመንት ሃሳብ ኮርፖሬሽኑ ከጀመረው ‘ቆሻሻን ወደሃብት’ የተሰኘ ፕሮግራም ጋር ተያያዥ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በተጨማሪም ኩባንያው ለሀገሪቱ ፅዱ ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ በመሆኑ በአፋጣኝ ወደ ቅድመ ኢንቨስትመንት ተግባር መግባት እንዳለበት አሳስበዋል።
ኩባንያው ያገለገሉ የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶችን በመሰብሰብ እና በመጠቀም ለኮንስትራክሽን የሚውሉ ግብዓቶችን የሚያመርት ነው።
በኮሎምቢያ፣ በሌሎች የላቲን አሜሪካ ሀገራት እና በኮትዲቯር ተመሳሳይ ግዙፍ ኩባንያዎችን በማቋቋም በስራ ላይ እንደሚገኝ ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ