
የኢትዮጵያንና የሩሲያን ታሪካዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁለቱ አገራት በትብብር እንደሚሰሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ከሩሲያ ፌዴሬሽን ፌዴራል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቫለንቲና ማትቬዬንኮ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
ውይይቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ የሰጡት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በሩሲያና በኢትዮጵያ መካከል ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን አንስተዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በአፈ-ጉባኤ ቫለንቲና ከተመራው ልዑክ ጋር ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በኃይል ዘርፍ፣ በኢንፎርሜሽን ደህንነት እና በመገናኛ ቴክኖሎጂ መስክ ያለውን ትብብር ማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት መደረጉን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል የተጀመረው ፓርላሜንታዊ ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩንም ጠቅሰዋል፡፡
የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መግባባት ላይ መደረሱን አፈ-ጉባኤ አገኘሁ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያና የሩሲያን ታሪካዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሩሲያ በረራ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ይህም ሰዎችና ምርቶችን ለማጓጓዝ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን አስረድተዋል።
የሁለቱን አገራት የንግድ እና የንግድ ዘርፍ ማህበራትን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች በቀጣይ እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ