ስረጃን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ መቅረፅና ውሳኔ መስጠት የሚያስችል የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ዛሬ ይፋ እንደሚደረግ የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ የዓለም የቱሪዝም ቀንን ለማክበር የሚዘጋጁ ሁነቶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተቀዋል።
በዓሉ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ይከበራል ብለዋል።
የዓለም የቱሪዝም ቀን በማስመልከት በሚከናወኑ መርሀ ግብሮች የኢጋድ አባል ሀገራት የቱሪዝም ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከ100 በላይ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
በነገው መርሀ ግብር ኢትዮጵያ ማስረጃን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ለመቅረፅና ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ ታደርጋለች ብለዋል።
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንቱ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቱሪዝም እንዲሁም የስታስቲክስ ክፍሎች፤ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የሳተላይት አካውንቱ መረጃዎችን ሰንዶ በማስቀመጥ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ አቅም አሟጦ መጠቀም የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
ቱሪዝም ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች አንፃር ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርት /GDP/ ያለውን ድርሻ እና የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ግብይት መጠኑን ለመረዳት የሚያስችል አካውንት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዛሬ ይፋ የሚደረገው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት አዘጋጅቶ ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ከ6 ወር ያህል ጊዜ መውሰዱን አመልክተዋል።
ከዚህም ባሻገር ኢጋድ እና አባል ሀገራቱ በቀጣናው ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን እውን ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀው የ10 ዓመት “ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላን” መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የኢጋድ አባል ሀገራት የቱሪዝም ዓውደ ርዕይ፣ የባለድርሻ አካላት እንዲሁም የአባል ሀገራት የሚኒስተሮች ስብሰባ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ይህን የቱሪዝም መድረክ ማዘጋጀቷ ሀገራት የቱሪዝም ሀብታቸውን እንዲያስተዋውቁና ትስስር እንዲፈጥሩ በር ይከፍታል ብለዋል።
የዓለም የቱሪዝም ቀን እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ1980 ጀምሮ በየ ዓመቱ መስከረም 17 በተለያዩ መርሀ ግብሮች ይከበራል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ