የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶው የጀመረው አዲስ በረራ የኢትዮጵያና የፖላንድን ትስስር ያጠናክራል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶው የጀመረው አዲስ በረራ የኢትዮጵያና የፖላንድን የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ለማጠናከር እንደሚያግዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖላንድ ዋርሶው ትላንት ማምሻውን አዲስ በረራ የጀመረ ሲሆን በረራውም በሳምንት አራት ጊዜ ይደረጋል ተብሏል።

በማስጀመሪያ መርኃ-ግብሩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ አመራሮች፣ በኢትዮጵያ የፖላንድ አምባሳደር ፕርዝማይዝለው ቦባክ እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚሁ ጊዜ፤ የበረራው መጀመር የሁለቱን አገራት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

ሁለቱ አገራት በቴክኖሎጂ በግብርና በመሠረተ-ልማትና ሌሎችም የትብብር መስኮች በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ዕድሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የዚህ በረራ መጀመር ሁለቱ ሀገራት ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት።

በረራው መጀመሩ ፖላንድን ከአፍሪካ ጋርም ይበልጥ ለማስተሳሰር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በፍጥነት እያሰፋ ባለበት ወቅት በፖላንድ አዲስ መዳረሻ መጀመር ተጨማሪ ስኬት ነው ብለዋል።

ይህም አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ውስጥ በተለይም በአውሮፓ ገበያ ያለውን ድርሻ ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።

የበረራው መጀመር የሁለቱን ሀገራት የኢንቨስትመንት፣ የንግድ ትስስር ለማሳደግና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከርም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የፖላንድ አምባሳደር ፕርዝማይዝለው ቦባክ በበኩላቸው፤ የበረራው መጀመር የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ይበልጥ ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *