የኢትዮጵያ እና የቻይና የንግድና ኢንቨስትመንት ትውውቅ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ሃሰን መሃመድ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የሥራ ሃላፊዎችና የቻይና የንግድ ም/ቤት ልዑክ ተሳትፈዋል።
አቶ ሃሰን መሃመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ኢትዮጵያና ቻይና ለረጅም ዓመታት የዘለቀ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት አላቸው።
ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ ልማትና በሌሎች ዘርፎችም በጋራ በመስራት ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የንግድና ኢንቨስትመን ትብብርን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና የዛሬው መድረክ አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የቻይና ልዑካን ቡድን ተወካይና የሲፒሲ ምክትል ፀሃፊ ሊዩ ዋይ በበኩላቸው÷ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ የልማት ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ትሰራለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ፣ በኢንዱስትሪና በግብርናው ዘርፍ በስፋት በመሰማራት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እየፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ