ተቀማጭነቱን በሩሲያ ፌደሬሽን ኦሪዮል ግዛት ያደረገ እና 17 ግዙፍ አምራች ኩባንያዎችን የያዘው የሩሲያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሊያመርት መሆኑን ገልጿል።
በፓርኮቹ ውስጥ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ የወሰነው ኩባንያ ከ10 ቢሊየን ሩፕል በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል እንዳስመዘገበ የተገለጸ ሲሆን÷ ኩባንያው አግሮ ግሩፕ ኢንቨስት የተሰኘ ነው።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ÷የኢንቨስትመንት ግሩፑን ዳይሬክተር ካትኮቭ ዴኒስና የስራ ባልደረቦቻቸውን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ ወቅት አቶ አክሊሉ ታደሰ÷ ኢንቨስትመንት ግሩፑ የደረሰበት ውሳኔ ትክክለኛ እና ጊዜውን የጠበቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተለይም ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ያዘጋጃቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ፖሊሲዎች እና ዘርፈ ብዙ ማበረታቻዎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል።
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ ኢንቨስትመንቱ እውን እንዲሆን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ካትኮቭ ዴኒስ በበኩላቸው÷በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የተሰማራው ግሩፕ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት ለማድረግ መወሰኑን ጠቅሰው÷ ኢንቨስትመንት ጥናቶችንና መረጃዎችን እያጠናቀረ መሆኑን አሳውቀዋል።
በሩሲያ የሚገኘውን ከፍተኛ የጋርመንትና ቴክስታይል ገበያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራች ኩባንያዎች መጠቀም እንዲችሉም ውይይት መደረጉን የኮርፖሬሽን መረጃ ያመላክታል።