የልማት ፈንዱ በአዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

የቻይና-አፍሪካ የልማት ፈንድ በኢትዮጵያ በሚገነባው አዲስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከቻይና-አፍሪካ የልማት ፈንድ ምክትል ፕሬዝዳንት ዩ ዡሩዊ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ እና ቻይና የጋራ ትብብር እድሎች እና ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

አምባሳደር ተፈራ ሀገራቱ ያላቸውን የቆየ አጋርነት ማጠናከር እና የኢንቨስትመንት ትብብር አማራጮችን ማስፋት እንደሚገባ አመልክተዋል።

አዲስ በሚገነባው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ንዋዩን ማፍሰስ የሚችልበት እድል እንዳለ አንስተዋል።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ልማት በማስመልከት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የልማት ፈንዱ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን እንዲቃኝ ጥሪ አቅርበዋል።

የቻይና-አፍሪካ የልማት ፈንድ ምክትል ፕሬዝዳንት ዩ ዡሩዊ የጋራ ምክክሮች የልማት ትብብር ለማጠናከር እና አዲስ የትብብር አማራጮችን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።

የልማት ፈንዱ በኢትዮጵያ አዲስ በሚገነባው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ ተሳትፎ የማድረግ ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለፈንዱ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ቢሮ አዲስ ተወካዮችን መመደቡንም ጠቁመዋል።

አምባሳደር ተፈራ መንግስት ለልማት ፈንዱ አዲስ ተወካዮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *