ግጭቶች የመንግስት የሀገር ብድር እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረጋቸዉን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል
የብድር ጫና፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የስራ አጥነት ማሻቀብ በአንድ ሀገር ውስጥ የማክሮኢኮኖሚ መዛባት መኖሩን የሚያሳዩ መገለጫዎች መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናራሉ።
ባለሙያዎቹ እንደሚገልጹት በኢትዮጵያ ውስጥ ለአመታት የዘለቀውን የማክሮኢክኖሚ መዛባት ለማስተካከል ስትራቴጂያዊ መፍትሄ ያሻዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ እና የሀገር ውስጥ አጠቃላይ ብድር 64.36 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፓርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት አስታውቀዋል።
አቶ አህመድ ሺዴ እንደገለጹት ከዚህ ውስጥ የውጭ ብድር 28.5 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የሀገር ውስጥ ብድር ደግሞ 35.8 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስረድተዋል።
ከአጠቃላይ የውጭ ብድር ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ድርሻ 20.1 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ድርሻ 8.4 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ አላቸው።
ከሀገር ውስጥ ብድር አንጻር ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ድርሻ 21.9 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ድርሻ 13.8 ቢሊዮን ዶላር ነው ተብሏል።
የሚኒስቴሩን ሪፖርት ያደመጠው ቋሚ ኮሚቴው የመንግስት የሀገር ውስጥ ብድር እየጨመረ በመምጣቱ በቀጣይ የተለየ ፖሊሲን በመከትል ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
አል ዐይን አማረኛ የመንግስት የሀገር ውስጥ ብደር መጨመር እና ምጣኔሀብታዊ አንድምታው ምንድነው? ሲል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን ሀሳብ ጠይቋል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዋሲሁን በላይ የበጀት ጉድለት ያለባቸው ሀገራት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ምንጮች ብድሮችን በመውሰድ ኢኮኖሚያቸውን መደጎም የተለመደ ቢሆንም የብድር ሁኔታው መመጣጠን ካልቻለ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው ይላሉ።
መንግስት ከልማት እና ከግል ባንኮች የቦንድ ሽያጭ (ትሬዤሪ ቢል) ማቅረብን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ከሀገር ውስጥ ብድሮችን መውሰዱ ጤናማ ቢሆንም የግል ሴክተሩ የሚንቀሳቀስበት የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ ግን ጫና እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ መንግስት የበጀት ጉድለት ለመሙላት ብድር ግድ ሲሆን ከውጭ ብድር የማግኘት እድሉ የተሻለ ስለሆነ በሀገር ውስጥ የሚቀሳቀሰውን ገንዘብ ለመበደር ከግል ሴክተሩ ጋር ሽሚያ ውስጥ መግባት የለበትም።
ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ እና ጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በተለያየ ግዜ ያወጣቸውን መመሪያዎች ተከትሎ ለግል ባለሀብቱ የሚሰጠው የብድር አቅርቦት ቀንሷል፡፡ ይህ ደግሞ የግል ሴክተሩ በሚገባው ልክ እንዳይንቀሳቀስ እና ለኢኮኖሚውም ጉልበት እንዳይሆን ይገድበዋል።
ባንኩ ይፋ ባደረገው ማሻሻያውን መሰረት ባንኮች ማበደር የሚችሉት ባለፈው አመት ካበደሩት 14 በመቶ እንዳይበልጥ እና ከብሔራዊ ባንክ ለሚወስዱት ብድርም ይጠየቁ የነበረውን የብድር ወለድ ከ16 ወደ 18 በመቶ ከፍ አድርጓል።
የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ እና በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶች የመንግስት ወጪ እንዲጨምር በማድረጋቸው የመንግስት የሀገር ውስጥ የብድር ምጣኔ ከውጭ ብድር እንዲበልጥ ሆኗል የሚሉት ደግሞ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ናቸው።
ተንታኙ “በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለሁለት አመታት የተደረገው ጦርነት ከፈጠረው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ባለፈ በመንግስት ገቢ እና ወጪ ላይ የፈጠረው መዛባት ገና ታክሞ አልዳነም” ባይናቸው።
ከዚህ ባለፈ ግጭቱን ተከትሎ ከውጭ አበዳሪ አካላት በብድር እና በድጋፍ ይገኝ የነበረው ድጋፍ በመቀነሱ መንግስት የሀገር ውስጥ ብድር ላይ እንዲያተኩር ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የ9ወራት ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ ፣ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከውጭ ዕርዳታ በበጀት ድጋፍ መልክ ይገኛል ተብሎ የታቀደው ገቢ እንደተጠበቀው አለመሆኑን ተናግረዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው “መንግሰት ያለበትን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ገንዘብ ከማተም ይልቅ የሀገር ውስጥ ብድርን በአማራጭነት መውሰዱ መጥፎ የሚባል ባይሆንም ብድሩን ወስዶ የሚሰራቸው ፕሮጄክቶች ግን ያስወጡትን ገንዘብ የሚመልሱ እና ገቢ የሚያስገኙ መሆናቸው ላይ ትኩረት ሊደረግ ይግባል” ብለዋል።
የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሽዋፈራሁ ሽታሁን ይህን በሚያጠናክረው ሀሳባቸው መንግስት ፕሮጄክቶችን በብድር ለመስራት ከመነሳቱ በፊት “ምን ያህል አንገብጋቢ ናቸው?፣ አዋጭነታቸው ምንድረስ ነው? እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኞቹ ናቸው?” የሚሉትን ጥያቄዎች በቅድሚያ ሊመልስ እንደሚገባ ይናገራሉ።
የማይጠቅም ፕሮጀክት የለም የሚሉት ተንታኙ “ነገር ግን የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ በመዲናዋ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በካፒታል በጀት የሚሰሩ ፕሮጄክቶች ከላይ የተጠቀሱትን መሰረታዊ የአዋጭነት ጥያቄዎች በበቂ መልሰዋል ብሎ ለመናገር እቸገራለሁ” ብለዋል።
መንግስት የሚገኝበትን የበጀት ጉድለት ለመሙላት የታክስ ገቢ አሰባሰብ ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ምክረ ሀሳባቸውን የሚለግሱት አቶ ዋሲሁን ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተሳትፎ ለግል ሴክተሩ በመልቀቅ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ ማስፋት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የግል ባልሀብቱን ያሉበትን የአሰራር ማነቆዎች በመፍታት፣ በጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በብድር እና በተለያዩ ማነቃቂያዎች በመደጎም በምጣኔ ሀብቱ ላይ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ ከተቻለ መንግስት ከእዳ ጫና የተላቀቀ በጀትን ማስተዳደር የሚያስችለው እንደሆነ ይገልጻሉ።
አቶ ሽዋፈራሁ የፕሮጀክቶች አስተዳደርን ከብልሹ አሰራር የጸዳ ማድረግ፣ እንዲሁም ለግጭቶች መፍትሄ በመስጠት የሰላም ሁኔታውን ማስተካከል ኢኮኖሚው የሚገኝበትን ጫና በግማሽ እንደመቀነስ ነው ብለዋል።
አሁንም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተፈጠሩ ግጭቶች የሚፈናቀሉ ለወትሮው እራሳቸውን መደጎም የሚችሉ አሁን ላይ ግን በመንግስት ድጋፍ ላይ ጥገኛ የሆኑ ዜጎች መበርከት ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቅ ነው ባይ ናቸው አቶ ሽዋፈራሁ።
“በመሆኑም ከተለያዩ ታጣቂዎች ጋር የሚደረገው ውግያ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በማድረግ መንግስት ወደ ልማት ስራዎች ፊቱን በማዞር ኢኮኖሚውን ማከም ላይ የቤት ስራውን ሊሰራ ይገባል” ሲሉ አቶ ሽዋፈራሁ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶችን በተመለከተ መንግስት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ፣ እንዲሁም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ፣ ወጪውን በመቀነስ የዕዳ ጫናውን ማቃለል በሚችልባቸው ፖሊሲያዊ አካሄዶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚጠበቅበትም እንዲሁ።
የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የ9 ወራቱን ዕቅድ አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት የሀገሪቱ አጠቃላይ ብድር ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነጻጸር 39.4 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
መንግሥት በ2016 በጀት ዓመት ለውጭና ለሀገር ውስጥ ብድር ክፍያ ለመፈጸም በዕቅድ ከያዘው 159.2 ቢሊዮን ብር ዕቅድ ውስጥ በዘጠኝ ወራት 104 ቢሊዮን ብር ክፍያ ለመፈጸም አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ መክፈል የተቻለው 24 ቢሊዮን ብር ለውጭና 40.7 ቢሊዮን ብር ለሀገር ውስጥ እንደሆነ በሪፖርቱ ተካቷል።
በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች በሚታየው አለመረጋጋት ለሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ መሆን በመንግሥት በጀት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ፣ በተለያዩ ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሪ የሚጠየቁ ሥራዎችን ለማከናወን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማጋጠሙ የፕሮጀክቶችን ትግበራ እያጓተተ መሆኑን ሚንስትሩ መግለጻቸው ይታወሳል።
ምንጭ፦ አል አይን