የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በፈረንሳይ የተለያዩ ከተሞች ተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከፈረንሳይ ኤሮኖቲካል ባለስልጣናት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ እና የፈረንሳይ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የአየር ትራንስፖርት ዳይሬክቶሬት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢማኑኤል ቪቬት ናቸው።
ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፓሪስ በተጨማሪ ወደ ሌሎች ከተሞች በሳምንት ሶስት ተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ እንደሚያስችለው የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል።
አየር መንገዱ በሳምንት ሰባት በረራዎችን ወደ ፓሪስ፣ ሶስት በረራዎችን ደግሞ ወደ ማርሴይ ያደርግ እንደነበር ተገልጿል።
ከዚህ በኋላ በተደረሰው ስምምነት መሰረት አየር መንገዱ ከፓሪስ ውጭ በሌሎች ከተሞች ያደርግ የነበረውን ሶስት በረራዎች በማሳደግ ስድስት እንዲሆን ተደርጓል ነው የተባለው።
ተጨማሪዎቹ ሶስት በረራዎችን በሚመለከት አየር መንገዱ በፈቀዳቸው መዳረሻዎች እንደሚሆንም ተገልጿል።
ቀደም ሲል አየር መንገዱ ወደ ፈረንሳይ የሚበር የካርጎ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዳልነበረው የተገለጸ ሲሆን÷ በስምምነቱ በሳምንት ሶስት የካርጎ ትራንስፖርት በረራ እንደሚደረግ የሀገራቱ የአቪዬሽን ባለስልጣናት ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።
በተጨማሪም ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎቹ በአቪዬሽን ዙሪያ የሚከሰት ብክለትን ለመቀነስ በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል ተብሏል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ