- ከ35 በላይ ተቋማት የሰነድ ይወገድልኝ ጥያቄ አቅርበዋል
አስፈላጊ ሰነዶችን በሕገወጥ መንገድ በራሳቸው አልያም በጨረታ የሚያስ ወግዱ ተቋማትን በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጽሐፍት አገልግሎት (ወመዘክር) አስታወቀ።
በአሁኑ ወቅት ከ35 በላይ ተቋማት ሰነዶቻቸው በሕጋዊ መንገድ እንዲወገድላቸው ለአገልግሎቱ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጽሐፍት አገልግሎት የተቋማትን ሰነዶች የማስወገድ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል፤ በትናንትናው እለትም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትንና የሙገር ሲሚንቶ ሰነዶችን በሕጋዊ መንገድ አስወግዷል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በተቋማት የሚገኙ የተለያዩ ሰነዶችን ለይቶ ያስወግዳል።
በሀገሪቱ ሰነዶችን የማስወገድ ሥራ የተሰጠው ለተቋማቸው ብቻ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን አንዳንድ ተቋማት ሕገወጥ በሆነ መልኩ ሰነዶችን በእራሳቸው አሊያም በጨረታ በማቅረብ እያስወገዶ መሆኑን አንስተዋል።
ተቋሙ እነዚህ ተቋማትን የማስተማር ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን ለማስተካከል ፍቃደኛ ያልሆኑ ተቋማት በሕግ አግባብ እንደሚጠየቁ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ለታሪክና ለነባር መረጃዎች ልዩ ትኩረት የምትሰጥ ሀገር ነች ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በየጊዜው የሚዘጋጁ ሰነዶች አገልግሎት ባይሰጡም እንኳን ለመዛግብትነት እንደሚቀመጡ ተናግረዋል።
ይወገዱልን ተብለው ወደተቋሙ የሚመጡ ሰነዶች በባለሙያዎች አማካኝነት ምስጢራዊነታቸው ተጠብቆ አይጠቅሙም ተብለው የሚለዩትን እንዲወገዱ በሌላ በኩል ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለታሪክ ይጠቅማሉ ተብለው የሚገመቱ ሰነዶች ደግሞ ወደ መዛግብት ክፍል እንዲገቡ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት ተቋሙ ሰነዶችን ለማስወገድ ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም ካለው አቅምና የቦታ ውስንነነት አንጻር ለበርካታ ጊዜያት ሥራውን ሳያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፤ በዚህ ምክንያት በርካታ ተቋማት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ተቋሙ ኃላፊነቱን ለመወጣት ተመሳሳይ ሥራ ከሚሠሩ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ የሰነድ አወጋገድ ሂደቱ ዘመናዊ በሆነ መንገድ እንደገና አገልግሎት መስጠት ወደሚችል ጥሬ እቃነት ለመቀየር እንደሚረዳ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተመጽሐፍት አገልግሎት የሥልጠናና ማማከር ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የሰነድ ማስወገድ ኮሚቴ ሰብሳቢ መኮንን ከፋለ በበኩላቸው፤ ሰነዶች በበዙ ቁጥር ሰፊ ቦታና የሰው ኃይል ስለሚጠይቁ አላስፈላጊ ሰነዶችን በማስወገድ ከአገልግሎቱ ጋር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በሰነዶች አወጋገድ ዙሪያ በግላቸው እንዲሁም ጨረታ አውጥተው የሚያስወግዱ ተቋማቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ተቋሙም ይህንን የማስተማርና የማስቆም ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል
ከ35 በላይ የሚሆኑ ተቋማት ሰነዶቻቸው በሕጋዊ መንገድ እንዲወገድላቸው መጠየቃቸውን ተናግረው፤ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት እንደሚገኙበት አስረድተዋል።
(ኢ ፕ ድ)