ጋምቤላ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ሺህ 747 ኪሎ ግራም በላይ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረጉን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ገለፀ።
ክንውኑ ከዕቅዱ በአራት ዕጥፍ ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ጊሎ እንደገለጹት፤ ከለውጡ ወዲህ የክልሉን ሰፊ የወርቅ ማዕድን ከብክነት በመታደግ ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው።
በሀገር በቀል ማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው የብዝሃ ኢኮኖሚ ትኩረቶች መካከል ማዕድን አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ በተሰጠው ትኩረትም እንደ ክልል ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በባህላዊ እና በወርቅ አምራች ኩባንያዎች ከ2 ሺህ 747 ኪሎግራም በላይ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ተልኳል ብለዋል።
አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አራት ዕጥፍ በላይ እንደሆነ ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ የወርቅ ልማት እና ከክልል እስከ ወረዳ የተጠናከረ የድጋፍና ቁጥጥር ስራዎች ለውጤታማ አፈጻጸሙ እንዳገዘ ተናግረዋል።
በቀጣይም ክልሉ አፈጻጸሙን በማጠናከር ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የሚያቀርበውን ወርቅ ምርት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ