በ2016 በጀት ዓመት ለኢንቨስትመንት የሚሆን 58 ሺህ ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱን የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ። በዘርፉ ለ500 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል።
የቢሮው ኃላፊ አሕመድ እንድሪስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ወደሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የሚያለሙበት 58 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የተዘጋጀው የኢንቨስትመንት መሬት በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች እንደሚተላለፍ ገልጸዋል።
በ2016 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን፣ አርሶ አደሮችን፣ ዩኒየኖችን፣ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በአጠቃላይ 30 ሺህ አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ለመቀበል ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ሦስት ወራት ውስጥ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ሁለት ሺህ 700 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ጥያቄ ማቅረባቸውን አመላክተዋል።
የቀረቡት የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በአገልግሎትና በሌሎች ዘርፎች ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፉት ጊዜያት 400 ባለሀብቶች በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም 206 ባለሀብቶች በግብርና ዘርፍ እንዲሰማሩ መደረጉን ገልጸዋል።
በሥራ ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 66 ነጥብ አምስት ለማሳደግ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አሕመድ፤ ከውጭ ሀገር የሚገቡ የተለያዩ ምርቶች በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲያመርቱ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
ወደውጭ ሀገር ከሚላኩ የኢንዱስትሪ ምርቶች 800 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፤ የምርቶችን ጥራት በመጨመር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፉ በአጠቃላይ ለ500 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸው፤ የተያዘውን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ ለባለሀብቶች የተለያዩ ግብዓቶችን ማቅረብ ከሚችሉ የፋይናንስ ተቋማትና ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ወደሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አሕመድ ገለጻ፤ በሥራ ላይ የሚገኙ ኢንቨስተሮችን የመደገፍና የመከታተል ሥራ እየተሠራ ሲሆን፤ ያለባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃ፣ የመሠረተ ልማት፣ የፋይናንስና የግብዓት ችግሮች በመለየት መፍትሔ እየተሰጠ ይገኛል።
በሥራ ላይ ከሚገኙት ኢንቨስተሮች መካከል 556ቱ ብድር፣ 16ዎቹ መብራት እንዲሁም 136 የሚደርሱት ደግሞ የተለያዩ ማሽኖችን እንደሚፈልጉ በመለየቱ ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ መቅረቡን አስታውቀዋል።
በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ያቆሙ 168 ኢንዱስትሪዎች ችግራቸውን በመለየትና ድጋፍ በማድረግ ወደሥራ እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢፕድ