በሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ እየሰራችበት ያለውን ከመተዳደሪያ ደንብ፣ ሕግ ነክ የሆኑ ጉዳዮችና የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓትን በተመለከተ ልምድ መቅሰም እንደሚፈልግ የጋቦን ሲቪል አቪዬሽን አስታወቀ።
በጋቦን ሲቪልአቪዬሽን ዳይሬክተር ጄኔራል ኤሪክ ትሪስታን የተመራ 14 አባላት ያሉት ልዑክ ከኢትዮጵያ ሲቪልአቪዬሽን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች መንግስቱ ንጉሴና ሚካኤል ተስፋዬ ጋር በሁለቱ ሀገራት ተቋማት መካከል በጋራ ሊሠሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በዚሁ ወቅትም ልዑኩ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር በጋራ ሊሰሩባቸው የሚችሉ የትብብር ሥራዎችን ለመቃኘት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አስታውቋል።
በዘርፉ ኢትዮጵያ እየሰራችበት ያለውን መተዳደሪያ ደንቦች፣ ሌሎች ሕግ ነክ የሆኑ ጉዳዮችንና የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓትን በተመለከተም ጋቦን ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግ መገለጹን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የኤርናቪጌሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር መንግስቱ ንጉሴ÷ ተቋማቸው በአየር ትራፊክ ቁጥጥርና የመገናኛ ናቪጌሽንና ቅኝት ዘርፎች ስልጠና በመስጠት የካበተ ልምድ እንዳለው ገልጸው ልምዱን ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በቀጣይም የጋራ የትብብር ሥራዎችን የሚያካትት የመግባቢያ ሠነድ ተዘጋጅቶ ውይይት ከተደረገበት በኋላ እንደሚፈረምና ወደ ሥራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ