ከአማራ ክልል 19 ሺህ 950 ኪሎ ግራም ኦፓልና ወርቅ ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል ተባለ

 በአማራ ክልል 19 ሺህ 950 ኪሎ ግራም የኦፓልና ወርቅ ማዕድናትን በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ እንደገለጹት÷ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክልሉን የማዕድን ሃብትና ፀጋ በጥናት በመለየት በስፋት እንዲለማ እየተደረገ ነው።

በዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ጥናቶችን በማከናወንና ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ በማድረግ የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ ሚናውን እንዲወጣ እያገዙ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ እንቅስቃሴ 19 ሺህ 950 ኪሎ ግራም የኦፓልና የወርቅ ማዕድናትን በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።

ማዕድኑ በባህላዊ መንገድ ተመርቶ የቀረበ መሆኑን በመግለጽ ቢሮው ሃብት በማፈላለግ፣ ወጣቶችን አደራጅቶ በማስገባትና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የማዕድን ሃብትና ፀጋን ለመለየት በተደረገ ጥረት እስካሁን ከ31 ሚሊየን ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ቦታ የሚሸፍን የማዕድን ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።

ወርቅ፣ ኦፓል፣ ሊትየም፣ ማንጋኒዝ፣ ኒኬል፣ ሰልፈርን ጨምሮ 40 የማዕድን ዓይነቶች መገኘታቸውን በጥናቱ ማረጋገጥ እንደተቻለ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *