ኢትዮጵያና ፓኪስታን በንግድ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በወጪና ገቢ ንግድ ዘርፍ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ በፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ሀገራት ዋና ኃላፊ አምባሳደር ሃሚድ አስጋር ከተመራ ልዑክ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነትን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያና ፓኪስታን ዘመናትን የተሻገር ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ሀገራቱ ባላቸው የህዝብ ብዛትና የማምረት ዕምቅ አቅም በትብብር ከሰሩ የላቀ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ የጋራ ግንዛቤ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

አምባሳደር ሃሚዲ የኢትዮጵያን የውጪ ንግድ ዕድገት አድንቀው÷ በቀጣይ ኢትዮጵያ ምርቶች በፓኪስታን ገበያ በስፋት እንዲቀርቡ ለማመቻቸት ቃል ገብተዋል ሲሉ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አመላክተዋል።

በሚቀጥለው ግንቦት ወር ፓኪስታን በአዲስ አበባ ለምታዘጋጀው ኤክስፖ ኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *