የኢትዮጵያ መንግስት ለፋይናንስ ተቋማት ባመቻቸው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የአክሲዮን ግዢ እድል መሠረት አዋሽ ባንክ የ70 ሚሊየን ብር አክሲዮን መግዛቱ ተገለጸ።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀሀይ ሽፈራው፥ “በካፒታል ገበያ የአክሲዮን አባል እንዲሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ቅድሚያ የተሰጣቸው በመሆኑ ባንካችንም ከአክሲዮን ግዢ በተጨማሪ የፕሮጀክት ቢሮ በማቋቋም ስራ ጀምሯል” ብለዋል።
በገበያ መር የኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ የካፒታል ገበያ መመስረትና ማደግ ለኢንቨስትመንት የሚሆን መዋዕለ-ነዋይን ማሰባሰብ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፖሊሲ ማዕቀፍ፣ የተፈጥሮ ሀብትና ወጣት የሰው ሀይል ቢኖራትም የካፒታል ውስንነት በመኖሩ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ቆይቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ነዋይ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ማቋቋም ይቻል ነበር ያሉት የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ-ነዋይ ገበያ ስራ አስኪያጅ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ናቸው።
ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማትና የውጭ ኢንቨሰተሮች እንዲሳተፉ በማሰብ መንግስት በአነስተኛ ድርሻ እንዲጀመር ማድረጉን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ-ነዋይ ገበያ በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ ተቋቁሞ በኢትዮጵያ ካሉ ተቋማት መካከል የፋይናንስ ተቋማት የአክሲዮን አባል እንዲሆኑ ቅድሚያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
በዚህም አዋሽ ባንክ የገዛው አክሲዮን ባንኩ የሰነደ መዋዓለ-ነዋይ ባለቤት ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።