አዲስ አበባ፡- ቻይና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ትፈልጋለች ሲሉ በአፍሪካ ኅብረት የቻይና ሚሲዮን አምባሳደር ሁ ቻንግቹን ተናገሩ፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልና የአፍሪካ ኅብረት ቀን በአፍሪካ ኅብረት የቻይና ሚሲዮን አዘጋጅነት ተከብሯል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት በአፍሪካ ኅብረት የቻይና ሚሲዮን አምባሳደር ሁ ቻንግቹን እንደገለጹት፤ ቻይና በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ዘርፎች ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት አላት።
ቻይናም ከአፍሪካ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ለማጠናከር በምታደርገው ጥረት የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ሥራ ታከናውናለች ሲሉ ተናግረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቻይና አፍሪካ የትብብር መድረክና የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የቻይና አፍሪካ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማሳደግና የባህል ልውውጦችን በማጎልበት ረገድ ዓይነተኛ ጠቀሜታ መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
በአፍሪካና በቻይና መካከል በተለያዩ መስኮችም የሚደረገው የኢኮኖሚ ትብብር አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።
ቻይናም ከአህጉሩ ጋር ዓለም አቀፍ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችንና ትብብርን ለማጠናከር እንደምትሠራ አስታውቀው፤ በቀጣይም ቻይና ለዓለም አቀፍ የሥልጣኔ ምንጭ የሚረዱ ሥራዎችን በመተግበር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሠረት ያደረገ አሠራርን እንደምትከተል ገልጸዋል።
ከአህጉሩ ጋር ያለውን ሁሉን አቀፍ የትብብር ልውውጦች፣ የጋራ መግባባቶችንና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን ለማጠናከር ቻይና እንደ ሁልጊዜው ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።
ቻይናም ሆነች አፍሪካ የሥልጣኔ መፍለቂያዎች ናቸው ያሉት አምባሳደሩ፤ በጊዜ ሂደት የተዋቀረ ታሪክ፣ ባህልና ድንቅ ጥበባዊ ቅርሶች እንዲሁም ሥልጣኔዎች ለሰው ልጅና ለዓለም ዕድገት የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
አምባሳደር ሁ ቻንግቹን እንዳመለከቱት፤ የዓለም ሥልጣኔን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ብዝሃነት መሠረት ያደረገ አሠራር ያስፈልጋል።
በተጨማሪ የሰው ልጅ የጋራ እሴቶችን በማስተዋወቅ፣ የሥልጣኔ ውርስና ፈጠራን በማበረታታት ለጋራ ዕድገት መሥራት ይገባል ብለዋል።
በዚህ መንገድ የአፍሪካውያንን አንድነትና አብሮነት በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን ማጎልበት እንደሚቻል አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት የአንድነትና የጥንካሬ ምልክት ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ኅብረቱ ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት ለማጠናከር የሚያከናውናቸው የትብብር ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ኅብረቱ ያዘጋጀው አጀንዳ 2063 ኢኮኖሚውን በማነቃቃትና የባህል ብልጽግናን በማሳደግ የአፍሪካውያንን አንድነት ለማጠናከር ይረዳል።
አምባሳደሩ ለመላው አፍሪካ ወዳጆች እንኳን ለአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመትና ለኢትዮጵያውያን 2016 አዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልና የአፍሪካ ኅብረት ቀን ሲከበር፤ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ትውልደ ቻይናውያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በዜጂያንግ ዉ ኦፔራ የምርምር ማዕከል የተዘጋጁና የቻይናውያንን የአኗኗር ዘይቤ የሚያሳዩ ኪነጥበባዊና ሙዚቃዊ ቴያትሮች ቀርበዋል።
ምንጭ፦ ኢ.ፕ.ድ