በሶማሌ ክልል እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ሥራዎች የሀገርን እድገት የሚደግፉ ናቸው።

በሶማሌ ክልል እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ሥራዎች የሀገርን እድገትና ምጣኔ ሃብት የሚደግፉ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።

የፌዴራል፣የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈጻሚዎች የጋራ የምክክር መድረክ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ማካሄዳቸው ይታወሳል።

ከምክክሩ በተጓዳኝ ኮሚሽነሩን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የሶማሌ ክልል የስራ ሃላፊዎች በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመነት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፥በክልሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ የኢንቨስትመንት ልማቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፈውበት በሁሉም መስክ በጥሩ አፈፃፀም ላይ መሆኑን ነው ያነሱት።

በዚህም ቀደም ሲል ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የተጀመሩ ጥረቶችን መደገፍ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተውበታል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችን የማሰቀጠልና የማስፋፋት እንዲሁም በዘርፉ ልማት የተሰማሩ ባለሃብተቶችን የመደገፍና ማበረታታት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ሥራዎች የሀገርን እድገትና ምጣኔ ሃብት የሚያግዙና የሚደግፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በከተማው የሚገኘው የስዎይስ ሞተር የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አብዲ ኢብራሂም፤ ፋብሪካው ተሽከርካሪዎችን እየገጣጠመ ለገበያ እያቀረበ መሆኑንና ለ300 ዜጎችም ቋሚ የስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሌላው በክልሉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል አቶ መሐመድ ከዲር፤ በ300 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያቋቋሙት የታሸገ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ በቀጣይ ሳምንት ስራ የሚጀምር መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ ልማት የመንግስት ማበረታቻ ጥሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይ ለተሻለ ስኬት የሚሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሶማሌ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አህመድ ረሺድ፤ በክልሉ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ዘርፉን ለማበረታታት የመሬት አቅርቦት፣ መሰረተ ልማቶችን የማሟላትና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታኅሣሥ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ተገኝተው ለሀገር ውስጥ ገበያ የጄቱር መኪናዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *