የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በቀን ውስጥ ማንቀሳቀስ የሚቻለው የገንዘብ መጠን ላይ ያነሳውን ገደብ በድጋሚ የሚጥል መመሪያ አዘጋጀ። ረቂቅ መመሪያው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞች በአካውንታቸው ውስጥ መያዝ የሚችሉትን የገንዘብ መጠን ከ100 እስከ 233 በመቶ አሳድጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው ይህ ረቂቅ የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድ አውጪነት ፈቃድ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ያለውን መመሪያ እና ማሻሻያዎቹን የሚተካ ነው። አሁን በስራ ላይ ያለው መመሪያ፤ በፋይናንስ ተቋማት ብቻ ተገድቦ የነበረውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ዘርፍ “ለፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋማት” (Fintech) የከፈተ ነበር።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አማካኝነት በየካቲት 2014 ዓ.ም. የተሻሻለው ይህ መመሪያ ደንበኞች በቀን ውስጥ ማዘዋወር በሚችሉት የገንዘብ መጠን ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ እንዲነሳ አድርጎ ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት ለባለድርሻ አካላት የተሰራጨው አዲሱ ረቂቅ መመሪያ ግን ዕለታዊ የገንዘብ ዝውውር መጠን ላይ በድጋሚ ገደብ የጣለ ሆኗል።
በኢትዮጵያ በብሔራዊ ባንክ የክፍያ እና የሂሳብ ማወራረጃ ሥርዓት ተጠባባቂ ዳሬክተር አቶ ሰለሞን ዳምጠው ተፈርሞ የተሰራጨው ይኸው ረቂቅ መመሪያ፤ የ“ደረጃ አንድ” ደንበኞች በአንድ ቀን ውስጥ ከ20 ሺህ ብር በላይ ማዘዋወር እንደማይችሉ አስፍሯል። በዚህ ደረጃ የተቀመጡ ደንበኞች፤ በአካውንታቸው ውስጥ መያዝ የሚችሉት የገንዘብ መጠን ከአምስት ሺህ ወደ 10 ሺህ ብር ከፍ እንዲልም ተደርጓል።
አዲሱ ረቂቅ መመሪያ በ“ደረጃ ሁለት” የተመደቡ ደንበኞች በቀን ውስጥ ማዘዋወር የሚችሉት የገንዘብ መጠን እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ መሆኑን አስቀምጧል። መመሪያው በዚህ ምድብ ያሉ ደንበኞች በአካውንታቸው ውስጥ መያዝ የሚችሉት የገንዘብ መጠን በ70 ሺህ ጨምሮ 100 ሺህ ብር አድርሶታል።
#Via Ethiopian Insider “