ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ክልሉ ካለው መልካ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ለወጪ ንግድ መር ኢንቨስትመንት ተመራጭ ነው

የሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአፋር ክልል ካላው ተፈጥሮ ሀብት እና መልካ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ምርት አቀነባብረው ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ለሚያቀርቡ ኩባንያዎች ተመራጭ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመን ጁነዲ ገለጹ።

ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጂቡቲ ወደብ ከ280 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከአሰብ ወደብ በ290 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ መገኘቱ ኤክስፖርት መር ለሆኑ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ፓርኩን እጅግ ተመራጭ እንደሚያደርጉ አቶ ዘመን ጁነዲ ጠቁመዋል።

የአፋር ክልል በግብርና ዘርፍ እና በተፈጥሮ ሀብት ረገድ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ሰላም እና ወጣት የሰው ሀይል ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የገቡ ባለሃብቶችን መሳብ መቻሉን አቶ ዘመን አብራርተዋል።

በፓርኩ ስራ ለመጀመር የሚያስችል የፋብሪካ ተከላ እና የሼድ ግንባታ እያከናወኑ ያሉ ባለሀብቶች አፋር ክልል የሚገኘውን ከፍተኛ የጨው ሀብት በፋብሪካ በማቀነባበር ለሰው እና ለእንሰሳት ምግብነት እንደሚያቀነባብሩ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

ፋብሪካዎቹ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን የጨው ምርት እንደሚያመርቱም ጨምረው ገልጸዋል።

መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማበረታታት የሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸዉ ልዩ ኢኮኖሚክ ዞኖች ዉስጥ ገብተው መዋለ ነዋያቸውን፣ የአስተዳደር እና የምርት ሰንሰለት እውቀታቸውን ለሚያጋሩ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ባለሀብቶች አበረታች ሁኔታ መፈጠሩን ጨምረው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሀገር ውስጥና የዉጭ ኢንቨስትመንት ፍላጎት እየታየ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማበረታታት ከዚህ ቀደም በነበረው 10 በመቶ የሊዝ ቅድመ ክፍያ ላይ በተለየ ሁኔታ ለሀገር ውስጥ ባላሀብቶች ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ከመደረጉ በተጨማሪም በዶላር የነበረውን ክፍያ በብር መደረጉንም ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ከሚገኙ 177 ያህል የማምረቻ ሼዶች ውስጥ ከ 86 በመቶ በላይ የሚሆኑት በውጭና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መያዛቸው ይታወቃል።

በሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክም አስፈላጊው መሰረተ ልማት የተሟላላቸው 5500 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው የማምረቻ ሼዶች አሁንም ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ሆነው ባለሀብት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *