በኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በህንድ ሪፐብሊክ መንግስታት መካከል የዲፕሎማቲክና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛ ለማስቀረት የተደረገውን ስምምነት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸደቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያ እና በደቡብ ኮሪያ እንዲሁም በህንድ ሪፐብሊክ መንግስታት መካከል የዲፕሎማቲክ እና ሰርቪስ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛ ለማስቀረት የተደረገውን ስምምነት አጽድቋል።
ከደቡብ ኮሪያ ጋር የተደረገው ስምምነት አዋጅ ቁጥር 1305/2016 ሆኖ የጸደቀ ሲሆን ከህንድ ሪፐብሊክ ጋር የተደረገው ስምምነትም አዋጅ ቁጥር 1306/2016 ሆኖ ጸድቋል።
በስምምነቱ መሰረት የዲፕሎማቲክ ወይም የሰርቪስ ፓስፖርት የያዙ የሁለቱ አገራት ዜጎች ለስራ ጉዳይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ቪዛ ለማግኘት የሚያስፈልጉትን ቅድመ-ሁኔታዎችና የሚወስደውን ጊዜ በማስቀረት የሚደረገው ጉዞ በቀላሉ እንዲመቻች ያደረጋልም ተብሏል።
ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ እና ከህንድ ሪፐብሊክ መንግስታት ጋር የሚኖራትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑም ተነስቷል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ በኢትዮጵያና በሊባኖስ መንግስታት መካከል በስራ ስምሪት ዘርፍ የተፈረመውን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅም መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መርቷል።
በኢትዮጵያ እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መንግስት መካከል በሁለትዮሽ ወታደራዊ ቴክኒካዊ ትብብር ወቅት የተገኙ የአዕምሯዊ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች እና ንብረቶች የጋራ ጥበቃ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅም መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲን ማቋቋሚያ ስምምነትም ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በኢትዮጵያ እና በፓኪስታን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግስታት መካከል የተፈረመውን የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነትም በተመሳሳይ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
ምንጭ፦ ኢ.ዜ.አ