በኢትዮጵያ ያደረግነው ጉብኝት የኢንቨስትመንት ዘርፉን በጥልቀት ለመቃኘት ዕድል ሰጥቶናል ሲል የሳዑዲ ዓረቢያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ከፍተኛ ልዑክ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለልዑኩ አባላት በቢሾፍቱ የሚገኘውን አለማ ካውዳይስ መኖ አምራች ድርጅት አስጎብኝቷል።
በጉብኝታቸውም በድርጅቱ የሚገኙ የተለያዩ ምርቶችንና ሂደቱን የተመለከቱ ሲሆን÷ ጉብኝቱ የኢንቨስትመንት ዘርፉን በጥልቀት ለመቃኘት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
ለሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረገው 79 አባላትን ያካተተው ልዑኩ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የጎበኘ ሲሆን÷ ከተለያዩ ሴክተሮች አመራሮች ጋርም መክሯል።
ትናንት ማምሻውንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር መወያየቱ ይታወቃል።
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ