የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ለከሰም ስኳር ፋብሪካ የሰራውን የጥናት ሰነድ አጠናቆ አስረከበ

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት የከሰም ስኳር ፋብሪካ የአዋጭነት ጥናት ሰነድን አጠናቆ አስረክቧል።

የጥናት ሰነዱን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ለከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታፈሰ ሻታ አስረክበዋል።

አቶ ሽፈራው በርክክቡ ወቅት እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በሀገራችን የሚገኙ 5 ትልልቅ ስኳር ፋብሪካዎች ያሉበትን ደረጃ ለማወቅና የተሻለ ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ ያለመ የአዋጭነት ጥናት ነው።

ከእነዚህም ውስጥ የ3 ስኳር ፋብሪካዎች ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለአስተያየት መላኩንና የከሰም ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ማስረከቡን ገልፀዋል።

የአዋጭነት ጥናቱ ፋብሪካው ያለበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የእድሳትና የማስፋፊያ ስራ ለመስራትና ለስራው የፋይናንስ ምንጭ የሚሆን ሰነድ የማዘጋጀትና ፋብሪካዎቹን ውጤታማ የሚያደርግ ጥናት ለመስራት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

አቶ ሽፈራው አክለውም ስኳር ፋብሪካው በተሰራው ጥናትና ግኝት ላይ ተመስርቶ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንደሚገባ ሙሉ እምነት አለን ብለዋል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታፈሰ ሻታ በበኩላቸው በተሰራው የአዋጭነት ጥናት የስኳር ፋብሪካው በመሉ አቅም ወደ ስራ እንዲገባና በአጭር ጊዜ ወደ ትርፋማነት እንዲመለስ እንደሚያግዛቸው ገልፀዋል።

ለጥናት ስራው መሳካት የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት አመራሮችና ባለሙያዎች ላደረጉት የተቀናጀ ስራ ምስጋና ማቅረባቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት በጥናትና ማማከር ዘርፍ የተለያዩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ላለፉት 40 ዓመታት እውን ያደረገ ተቋም ሲሆን አሁንም ከትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ጋር በጋራ እየሰራ የሀገር ልማት አጋርነቱን እያስመሰከረ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *