የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 10ሩ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አደጉ

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል 10ሩ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸውን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮቹና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና መካከል 10ሩ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኮርፖሬሽኑ ማሳወቁንም አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ፓርኮቹ ያሉበትን ደረጃ በመገምገም ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንነት ለማደግ 10ሩ አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላታቸው ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንነት እንዲያድግ መወሰኑም ተገልጿል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንነት ማደጋቸው የግል ዘርፉ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በአገልግሎት እና ሌሎች ልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሳተፉ ለማበረታታት፣ የሀገሪቱን የውጪ ባለሀብት ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ እንቅስቃሴ ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ክላስተሮችን ለማስተዋወቅ ሚናው ከፍተኛ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ ንግድን፣ ዕቃን ወደ ውጭ የመላክ አፈፃፀም እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት አቅም ለማሳደግ፣ በዓለም ዓቀፍ የንግድ ሰንሰለት የሚኖር ቁርኝትን ለማስፋፋት፡ እና ዘላቂ ዕድገት ለማምጣት የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆንም በመረጃው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ሥርዓት መፍጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ እርምጃዎችና የንግድ ሥርዓቱን ኢትዮጵያ ከገባችባቸው ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ የንግድ ሥርዓት ግዴታዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ነፃ ለማድረግ የምታደርገውን ጉዞ ለማገዝና የተመቻቸ የኢንቨስትመንት እና ንግድ አገልግሎት ሥርዓት በመፍጠር የሀገሪቱን የዓለም ዓቀፍ እሴት ሰንሰለት ተሳትፎ ለማጎልበት እና በቀጠናዊ ንግድ ውጤታማ በሆነ መንገድ፡ በጊዜ እና በወጪ የመወዳደር አቅምን ለማጠናከር እንዲሁም የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለማሳደግ አዋጅ ቁጥር 1322/2016 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ያደጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮችም አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ደብረ ብረሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *