የኢትዮ-ሳዑዲ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም መካሄድ ጀመረ

 የኢትዮ-ሳዑዲ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በፎረሙ ላይም የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ መካከል ታሪካዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት መኖሩን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ 2ኛውን ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መተግበር መጀመሯንም አስታውቀዋል።

መንግሥት የንግድ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉን ያስረዱት ሚኒስትሯ፥ ከሕግ፣ አሠራርና መሰረተ-ልማት አኳያም የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚያበረታታ ምቹ ምኅዳር መኖሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም የሳዑዲ ባለሀብቶች በማምረቻ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ታዳሽ ኃይልና በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሳዑዲ ዓረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን የተመራ 79 አባላትን የያዘ ከፍተኛ የኢንቨስትመንትና የንግድ ልዑክ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።

ልዑኩ ከፎረሙ አስቀድሞ የኢትዮጵያን የቆዳ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ማዕድንና ሌሎች ምርቶችን እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚያሳይ ዐውደ-ርዕይ ጎብኝቷል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *