የኢትዮጵያ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ የተፈራረሙት የፋይናንስ ልማት ትብብር ስምምነት የአገራቱን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኮሪያ ሪፐብሊክ ሴኡል ገብተዋል።
በዛሬው እለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኮሪያው ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ይኦል ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም የኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት ለኢትዮጵያ ልማት የፋይናንስ እገዛ ማድረግን ጨምሮ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን ማጠናከር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ግብርና ልማት ዙሪያ ይበልጥ ተቀራርበው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል ብለዋል።
ከመሪዎቹ ውይይት በኋላም ለአራት አመታት የሚተገበር የ1 ቢሊየን ዶላር የልማት ፋይናንስ ትብብር ስምምነት መፈረሙን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በተደረሰው ስምምነት መሰረትም ገንዘቡ ለመሰረተ ልማት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ፣ ለጤና እና የከተማ ልማት የሚውል ይሆናል ነው ያሉት።
የፋይናንስ ልማት ትብብር ስምምነት የአገራቱን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
የአሁኑ የልማት ፋይናንስ ትብብር ስምምነቱ የኮሪያ ሪፐብሊክ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ይኦል በኢትዮጵያ በቀጣይ የስራ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆኑን አረጋግጠዋል ብለዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ