የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፉት አስር ወራት 328 ሺህ 302 አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት 600 ሺህ ደንበኞችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን በማስታወስ ባለፉት 10 ወራት በተሰሩ ስራዎች 328 ሺ 302 አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የእቅዱን 65 ነጥብ 5 ከመቶ ማሳካት መቻሉን በመግለጽ በተመሳሳይ ወቅት 76 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በአስር ወራት የገጠር ከተሞች የኔትወርክ ማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል።
በቀጣይም የኤሌትሪክ ኃይል ያላገኙ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮችን እንዲሁም ደንበኞችን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ የኃይል መቆራረጥንና የኃይል ብክነትን ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
አገልግሎቱ በኤሌትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ውድመት እና ስርቆት በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት እንዲቀጡ ማድረጉን ተናግረዋል።
በዚህም አገልግሎቱ በ10 ወራት የመሰረተ ልማት ስርቆት የፈጸሙ 32 ግለሰቦች ከ 5 ወር እስከ 12 አመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ