የኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከመጪው ጥር ወር 2017 ጀምሮ በይፋ ስራ እንደሚጀምር የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን ኢስማኤል (ዶ/ር) ተናገሩ።
ገበያው በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የምጣኔ ኃብትና የፋይናንስ ፍላጎት አማራጭ እንደሚሆንም ተገልጿል።
ተቋሙ ባለፈው አንድ ዓመት ኩባንያውን ዕውን ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ ስራ ለመጀመር የሚያስችለውን ካፒታል የማሰባሰብ፤ የሰው ኃይል የማደራጀት ስራ ማከናወኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የገበያውን መተዳደሪያ ደንቦች የማዘጋጀትና ለህዝብ የማስተዋወቅ ስራን ጨምሮ ገበያውን በቴክኖሎጂ ለመምራት የሚያስችል ግዥ መፈፀሙን አመልክተዋል።
ገበያው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ፣ ግዥ እና ልውውጥ በቋሚነት የሚደረግበት ሲሆን ለመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ለምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መጀመር መንግስት እና የግሉ ዘርፍ ለሚያከናውኗቸው ኢንቨስትመንቶች ካፒታል ለማሰባሰብ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን ኢስማኤል (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አክስዮን የሚሸጡ ኩባንያዎች በየጊዜው የሂሳብ ሁኔታቸው እየተገመገመ ይፋ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።
አክሲዮን የሚገዙ አካላት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ግብይት ለማከናወን የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ