ባለፉት ዘጠኝ ወራት 30 ቢሊየን ብር ለአምራች ኢንዱስትሪው ብድር መስጠቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ከሚሰጠው ብድር 50 በመቶ የሚሆነው ለኢንዱስትሪዎች መሆኑን አስታውቋል።
ከኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ጎን ለጎን “የግል ኢንቨስትመንት እና አስቻይ ሁኔታዎች” በሚል የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባንኩ መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው የትኩረት መስኮች ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ በዝቅተኛ ወለድ ብድር በመስጠት የዘርፉን ተዋንያን እየደገፈ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ባንኩ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንደነበር ገልጸው፤ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከነበረበት ችግር ማውጣት መቻሉን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ባንኩ በዓመት እስከ 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ትርፍ እያገኘ መሆኑንም ፕሬዚደንቱ አንስተዋል።
አሁን ላይ የባንኩ ካፒታል 38 ቢሊየን ብር መድረሱንና ለአንድ ፕሮጀክት እስከ 9 ቢሊየን ብር ድረስ ማበደር የሚችልበት አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ 44 ቢሊየን ብር ብድር ማጽደቁን ገልጸው፤ ከዚህም 30 ቢሊየን የሚሆነው ለአምራች ዘርፉ የተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም እያደገ የመጣ ኢኮኖሚ መኖሩንና ባንኩ ራሱን በማሻሻሉ ለዚህ የሚሆን አቅም መፍጠሩን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ባንኩ ለዘርፉ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው፤ ንግድ ባንክ በከፍተኛ ሁኔታ አምራች ዘርፉን እየደገፈ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ባንኩ አጠቃላይ ለብድር ከመደበው ካፒታል ውስጥ 50 በመቶውን ወይም 550 ቢሊዮን ብር ለኢንዱስትሪዎች መስጠቱን ተናግረዋል።
ከዚህም ውስጥ 90 ነጥብ 6 በመቶው ብድር የረዥም ጊዜ ብድር መሆኑን አመላክተዋል።
የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።
ባንኩ በከፍተኛ ሁኔታ ዘርፉን እየደገፈ መሆኑን እና በአሠራር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፈተሽ የማሻሻል ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ