የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሱዳን የቴሌኮም ግሩፖች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

በኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል መካከል የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ ስትራቴጂያዊ አጋርነት በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል።

የሀገራቱ የቴሌኮም ግሩፖች አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር ከፍተኛ አቅም ባለው የፋይበር ኮኔክቲቪቲ ለማስተሳሰር የሚያስችል “የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ” የአጋርነት ስምምነት በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።

በተጨማሪም ስትራቴጂያዊ አጋርነቱ የቀጠናውን የዲጂታል መሠረተ ልማት ስብጥር የሚቀይር እጅግ አስተማማኝ እና የላቀ ኮኔክቲቪቲ መፍጠር የሚያስችል ከፍተኛ አቅም ያለው የመሬት ውስጥ ፋይበር ኦፕቲክ መሰረተ ልማት በመዘርጋት የአፍሪካን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ነው ተብሏል።

ኢኒሼቲቩ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጂቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል የጋራ መሠረተ ልማትና ዕውቀታቸውን በመጠቀም አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ ከፍተኛ አቅም (መልቲ ቴራቢት) ያለው አማራጭ የፋይበር መስመር እንዲዘረጉ የሚያስችል መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መረጃ አረጋግጧል።

እንዲሁም ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ተቋማት እና ግለሰቦች አማራጭ እና አስተማማኝ ኮኔክቲቪቲ እንዲኖራቸው፣ የኢንተርኔት መዘግየት ችግርን ለመቀነስ እና ከፍተኛ ፍጥነት የሚሹ የተሻሉ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *