ላለፉት አምስት ዓመታት ግንባታው የዘገየውን የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ከቻይና ሁናን ግዛት ቻንግሻ ከተማ ከመጡ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑካን ቡድን አባላት ጋር የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ማስጀመር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በውይይታቸውም የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ለማስጀመር ባለፈው አንድ ዓመት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ አክሊሉ አስረድተዋል።
በዚህም የወሰን ማስከበር፣ የይዞታ ማካለልን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ የቅድመ ግንባታ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም አረጋግጠዋል።
የሁናን ግዛት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ው ዣዎሹ በበኩላቸው የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታን ለማስጀመር የሚያስችል ልዩ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀው÷ ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማስጀመር ርብርብ እንደሚደረግ መናገራቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል።
የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክ በ108 ሔክታር ላይ የሚያርፍ እና በቻይናውያን ባለሀብቶች የሚገነባ ሲሆን÷ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በተለያዩ ዘርፎች ከ25 ሺህ ለሚልቁ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቅሷል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ