
የአሜሪካ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ያለውን ምቹ ሁኔታ እንዲጠቀሙ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም ገለጹ።
አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም በዌስት ቨርጂኒያ የምትገኘውን ሞርጋንታውን ከተማን ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና ምርምር፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም በባህል ልውውጥ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
አምባሳደር ብናልፍ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሙሉ አቅም እየተገበረች የምትገኘውን የኢኮኖሚ ማሻሻያን በተመለከተ ለአምራቾች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ ምቹ ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል።

የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመመልከት ወደ ኢትዮጵያ ለሚሄዱ አሜሪካውያን ኢንቨስተሮች ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ከኢኮኖሚው ባሻገርም በትምህርቱ መስክ ጉድኝቶችን በመፍጠር በባዮ ቴክኖሎጂ፣ በማህበረሰብ ጤና አና በመሳሰሉት ዘርፎች የፕሮግራም ልውውጦች እና የጋራ ትብብር ለማድረግ ከዌስት ቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አመራር እና አባላት ጋር የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል።
በአጠቃላይ ጉብኝቱ በኢንቨስትመንት ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን አማራጮች ማስተዋወቅ መቻሉ ተመላክቷል።
በትምህርቱ ዘርፍ በዌስት ቨርጂኒያ የሚገኙ ተቋማት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ለማስተሳሰርና ትብብሮችን ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚን መፍጠሩን ነው ኤምባሲው ያስታወቀው።
ምንጭ፦ ኢዜአ