የአለም ሀገራት ብድር 97 ትሪሊየን ዶላር መሻገሩን የመንግስታቱ ደርጅት አስታወቀ

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ያለባቸው ብደር ከአለም አቀፉ የብደር ምጣኔ አንድ ሶስተኛውን ይሸፍናል

መንግስታት ያለባቸው ብድር ከ2022 አመት አንጻር ሲወዳደር በ5.6 ትሪሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል

በ2023 በአለም አቀፍ ደረጃ የሀገራት ብድር 97 ትሪሊዮን ዶላር መሻገሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

የመንግስታቱ ደርጅት የንግድ እና ልማት ኤጄንሲ ባወጣው ሪፖርት የብድር ወለድ ምጣኔ ከፍተኛ መሆን ሀገራት ብድሩን ለመክፈል የሚደርጉትን ጥረት አክብዷል ነው ያለው።

ኤጄንሲው እንደገለጸው መንግስታት ያለባቸው ብድር ከ2022 አመት አንጻር ሲወዳደር በ5.6 ትሪሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል።

በዚህ የተነሳም በተለይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ትምህርት፣ጤና፣ መንገድ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶቻቸቸውን በማስኬድ እና ብድሩን በመክፈል መካከል ተወጥረዋል ነው የተባለው።

የ3.3ቢሊየን ህዝብ መገኛ በሆኑት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ከሶስቱ አንዱ ለመሰረተ ልማት ከሚያወጡት ይልቅ ብድሮችን ለመክፈል የሚበጅቱት ገንዘብ ይልቃል።

 በነዚህ ሀገራት በ2023 የነበረው የብድር መጠን 29 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን የአለም አቀፍ መንግስታት የብድር ጫናን 30 በመቶ ይጋራሉ።

ከኮሮና መከሰት በኋላ በቅጡ ባላገገመው የአለም ምጣኔ ሀብት የወረርሽኙን ማብቃት ተከትሎ የተፈጠሩ ጦርነቶች እና ሌሎች ጂኦፖቲክሳዊ ውጥረቶች የብድር ጫና እንዲያሻቅብ ምክንያት መሆናቸው ተነግሯል።

አሜሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የመንግስት ብድር ካለባቸው ሀገራት በ33 ትሪልዮን ዶላር ቀዳሚዋ ስትሆን ቻይና በ15 ትሪሊዮን ዶላር፣ ጃፓን በ10.6 ትሪልዮን ዶላር በደረጃ ይከተሏታል።

ከአፍሪካ ግብጽ በ377 ቢልዮን ዶላር ፣ደቡብ አፍሪካ በ279 ቢልዮን፣ናይጄሪያ በ173 ቢልዮን ዶላር የመንግስት ብድር በደረጃ ተቀምጠዋል።

 በአፍሪካ ያለው የብድር ምጣኔ የአህጉሪቷን አጠቃላይ የሀገረ ውስጥ ምርት እድገት 62 በመቶ እንደሚሸፍን የገለጸው ሪፖርት በአህጉሪቷ አስቸኳይ የብደር መክፈያ ጊዜ ማስተካከያ እና ሌሎች መሻሻያዎች ካልተደረጉ ምጣኔ ሀብቱ መሸከም ከሚችለው በላይ ጫናን ሊያስተናግድ ይችላል ተብሏል።

ከብደር ጫናው ባለፈ የወለድ ምጣኔው ለብዙ ሀገራት እራስ ምታት ሆኗል ያለው ተመድ በባለፈው አመት አጠቃላይ የብድሮች የወለድ ምጣኔ 847 ቢሊዮን ዶላር መሻገሩን ነው የገለጸው።

አሜሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ እያሻቀበ የሚገኝውን ብድር ጫና በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ ለመቀነስ የባለ ብዙ ወገን የገንዘብ ተቋማት የብድር እፎይታ እና የመክፈያ ግዜዎችን እንዲያራዝሙ መጠየቋ ይታወሳል።

በተጨማሪም አይኤም ኤፍ እና የአለም ባንክን ጨምሮ ለተለያዩ የገንዘብ ተቋማት 21 ቢልየን ዶላር ያበደረች ሲሆን ይህ ገንዘብ በድሀነት እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ይውል ዘነድ ያለ ወለድ የሚሰጥ ገንዘብ ነው።

ምንጭ፦ አል አይን

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *