
የቻይና ባለሀብቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የፈጠራቸውን እድሎች በመጠቀም በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ከቻይና ሕዝብ የፖለቲካ ምክክር ጉባኤ ብሔራዊ ኮሚቴ ምክትል ሊቀ መንበር እና የቻይና የኢንዱስትሪና የንግድ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ጋኦ ዩንሎንግ ከተመራ ልዑክ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ቻይናውያን ባለሀብቶች ቀዳሚ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ ከ3 ሺህ 500 በላይ ቻይናውያን 9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ በማድረግ በኢንቨስትመንት እንደተሰማሩ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚ ልማት እና የንግድ ትብብርን ይበልጥ ለማጠናከር፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የቻይና ባለሀብቶች በመጪው ግንቦት 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም በሚደረገው የኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ ፎረም ላይ እንዲሳተፉ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የቻይና ሕዝብ የፖለቲካ ምክክር ጉባኤ ብሔራዊ ኮሚቴ ምክትል ሊቀ መንበር እና የቻይና የኢንዱስትሪና የንግድ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ጋኦ ዩንሎንግ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የልማት እንቅስቃሴ አድንቀዋል።
የቻይና የንግድ ማህበራት በኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
የቻይና መንግስትም ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የኢንቨስትመንት፣ የኢኮኖሚ ልማት እና የንግድ ትብብርን ይበልጥ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለውም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ልዑኩ በተለያየ ዘርፍ ከተሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጉን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ፦ ኢዜአ