ኩባንያው በ2024 አራት ሚሊዮን መኪኖችን ሸጧል
ቢዋይዲ በ2025 ስድስት ሚሊዮን መኪኖችን የመሸጥ እቅድ እንዳለውም አስታውቋል
የቻይናው ቢዋይዲ ኩባንያ ፎርድ እና ሆንዳን በመብለጥ የዓለማችን ቁጥር አንድ መኪና ሻጭ ተባለ።
በቻይናዋ ሸንዘን ማዕከሉን ታደረገው ቢዋይዲ የመኪና አምራች ኩባንያ አሁን ላይ በመኪና ሽያጭ የዓለማችን ቁጥር አንድ መሆን ችሏል።
ኩባንያው የ2024 ዓመት ውስጥ ባሉት 11 ወራት ውስጥ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን መኪኖችን ሸጧል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ኩባንያው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ላለፉት ዓመታት ቀዳሚ የነበሩት የጃፓኑ ሆንዳን እና የአሜሪካውን ፎርድ ኩባንያዎችን በልጧል፡፡
በህዳር ወር ውስጥ ብቻ ከ500 ሸህ በላይ ቢዋይዲ ስሪት መኪኖች የተሸጡ ሲሆን ይህም ሌላኛው የዓለማችን ቁጥር አንድ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች የሆነው ቴስላ ኩባንያንም መብለጥ ችሏል፡፡
አለም አቀፍ የመኪና አምራቾች እና የገበያ ድርሻቸው ምን ይመስላል?
በቻይና በህዳር ወር ውስጥ በቻ የተሸጡ መኪኖች ቁጥር ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሆነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የቢዋይዲ ድርሻ ትልቁ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ቢዋይዲ ኩባንያ በዚህ እየተጠናቀቀ ባለው የ2024 ዓመት ውስጥ ለ200 ሺህ ዜጎች አዲስ የስራ እድል ፈጥሯልም ተብሏል፡፡
ኩባንያው በሚቀጥለው የፈረንጆቹ 2025 ዓመት ውስጥ እስከ 6 ሚሊዮን መኪኖችን ለዓለም ገበያ ለመሸጥ ማቀዱ ተገልጿል፡፡
ቢዋይዲ ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ሶስት ወራት ውስጥ 28 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዋጋ ያላቸው 1 ነጥብ 3 መኪኖችን በመላው ዓለም ሸጧል ተብሏል።
በመላው ዓለም ያለው የመኪና ሽያጭ ኢንዱስትሪ እድገት አሳይቷል የተባለ ሲሆን በተለይም በከፊል በነዳጅ እና በኤሌክትሪክ ወይም ሀይብሪድ የሚባሉት መኪኖች ተፈላጊነታቸው ጨምሯል ተብሏል።
ምንጭ፦ አል አይን