የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮ-ቱርክ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በኢስታንቡል ተካሂዷል።
አምባሳደር ምስጋኑ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በኢትዮጵያ በርካታ የቢዝነስ ዕድሎች መኖራቸውን አስገንዝበዋል።
የሁለቱ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገርም የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ በርካታ ዘርፎችን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት አድርጋለች ማለታቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስንትመንት ሆልዲንግ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሃብረቢ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና እንቅስቃሴ፣ ማበረተቻዎች እንዲሁም አዳዲስ ሕጎችን አብራርተዋል።
እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት የንግድ እንቅስቃሴ በሚመለከት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ውቤ መንግስቴ ገለጻ አድርገዋል።
የቱርክ ንግድ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሙስጠፋ ቱዝሁ እና የቱርክ የንግድ ማኅበረሰብ ማኅበር ፕሬዚዳንት ማህመት አስማሽ በኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት እና የንግድ አማራጮች መኖራቸውን በመግለጽ÷ ሰፊ ገበያ ባለት የአፍሪካ መዲና ኢንቨስት ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
ይህን በመገንዘብም የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ