የሳዑዲ ጎልድ ሪፋይነሪ ኩባንያ (Saudi Gold Refinery Co) በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ስራ ለመጀመር የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ።
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ከኩባንያው ባለቤት ሱሌይማን ሳሌህ አሎታይም ጋር በሪያድ ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኩባንያው በኢትዮጵያ ማዕድን ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
አምባሳደር ሙክታር፥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ያላት ሃገር መሆኗንና መንግስት በዘርፉ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ጨምሮ ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር ለመፍጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኩባንያው በዘርፉ ያለውን ልምድ እና ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ኤምባሲውም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
የሳዑዲ ጎልድ ሪፋይነሪ ኩባንያ (Saudi Gold Refinery Co) ሱሌይማን ሳሌህ አሎታይም ኩባንያቸው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።
ኩባንያው በማዕድን ዘርፍ ስራውን ለማስጀመር የሚያስችል እንቅስቃሴ እንደጀመረ መግለጻቸውን በሪያድ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ፦ ኢዜአ