የሩሲያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ያላቸውን ረጅምና በፈተና ያልደበዘዘ ጠንካራ ወዳጅነት የሚመጥን የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲኖራቸው መስራት እንደሚያስፈልግና ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው ኤምባሲያቸው አዳዲስ የሩሲያ ባለሀብቶች በግብርና፣ በአዉቶሞቢል አሴምብሊና ሌሎችም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በስፋት እየሰራ መሆኑን አስታውሰዋል።
በቅርቡም በድሬዳዋ የነፃ ንግድ ቀጠናና ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመግባት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን የጠቆሙት አምባሳደሩ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በሚቀርብ ስታንዳርድ መሰረተ ልማቶች ለኢንቨስተሮቹ ምቹ መሆናቸውንና በጋራ በመስራት ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አሳውቀዋል።
በኤምባሲው እና ኮርፖሬሽኑ መካከል ከተደረገው ኢንቨስትመንት ተኮር ውይይት ጎን ለጎን የኮርፖሬሽኑን አመራሮችና ሰራተኞች ሁለንተናዊ አቅም ለማሳደግ አጫጭርና የረጅም ጊዜ የትምህርትና የስልጠና ፕሮግራሞች በሚመቻቹበት አግባብ ላይ ከስምምነት ተደርሷል።