የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ መፈቀድ ለኢትዮጵያ ስታርት አፖች እድገት የተሻለ ዕድል ይዞ መምጣቱን የኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ጥላሁን እስማዔል ለኢዜአ እንዳሉት ካፒታል ገበያና ስታርትአፕ ተመጋጋቢ ዘርፎች ናቸው።
በዓለም የታወቁ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከጀማሪ ስራ ፈጣሪነት እንደተነሱ በማውሳት፣ ከዛሬ ቁመናቸው እንዲደርሱ ምቹ ሁኔታዎች እንደተፈጠረላቸው አንስተዋል።
በዲጂታል ዘመን በተለይም በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ስታርትአፕ ማጠናከር የአንድ ሀገር የወደፊት ተስፋና ዕድገት አይተኬ ሚና እንዳለው ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
በዚህም ሁለቱ አካላት እርስ በርስ የሚመጋገቡና የሚደጋገፉ ዘርፎች እንደሆኑ ገልጸዋል።
በአሁኗ ኢትዮጵያ የስታርት አፖች በመንግስት በኩል ትልቅ የፖሊሲ ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚደረግላቸው ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ በኢትዮጵያ መፈቀዱ ደግሞ ለስታርት አፖች ትልቅ ተሰፋና ዕድል እንደሆነ ገልጸዋል።
ለስታርት አፖች ከፋይናንስ ተቋማት የካፒታል እና የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ማግኘት ትልቁ ማነቆ እንደነበር ገልፀው፤ የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ መጀመር ግን ይህን ማነቆ በዘላቂነት እንደሚፈታ ገልፀዋል።
ይህም ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች በሃሳባቸው ብቻ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸው፣ በሌላ በኩል በካፒታል ገበያው ስታርትአፕ ሁነኛ ተዋናይ እንዲሆኑ ያስችላል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል የሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ መጀመር በኢትዮጵያ ትልቅ ተግዳሮት በሚወሳው የፋይናንስ የአካታችነት ችግር ለማቃለልም አዎንታዊ አበርክቶ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
በተለይም ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ከካፒታል ባሻገር በየጊዜ የሚያጋጥማቸውን የስራ ማስኬጃ ገንዘብ በተለያዩ ሰነዶች በመገልገል ተጠቃሚ እንዲሆኑም እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኢንቨስመንት ባንክ መጠናከር ለንግድ ባንኮች የተለያዩ ሰነዶችን በመሸጥ የተቀማጭ ገንዘብ አቅማቸው እንዲጎለብት እና የፋይናንስ ምህዳሩ እንዲሳለጥ ያግዛልም ብለዋል።
በተዘዋዋሪ በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ የማህበረሰብ ክፍልን ለመድረስ እንደሚረዳም አንስተዋል።
በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ወራት ይፋዊ ስራ እንደሚጀመር በሚጠበቀው የኢትዮጵያ ሠነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ከፋይናንስ አካታችነት ባሻገርም የብዝሀ ኢንቨስመንት አማራጭ ዕድል እንዲሰፋ ያስችላል ብለዋል።
ይህም በርካታ የማህበረሰብ ክፍል ወደ ግል ከሚዛወሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የአክሲዮን ባለቤት እና የትርፍ ተቋዳሽ በማድረግ ረገድ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ነው የገለጹት።