የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር የጭነት መርከቦች ላይ በሚፈጸሙት ጥቃት ሳቢያ፣ ትልልቅ የመርከብ ኩባንያዎች ወደ አካባቢው ስለማይመጡ፣ ኤክስፖርተሮች ከባድ ችግር ውስጥ መውደቃቸውንና በሥራቸው ላይም መስተጓጎል እየገጠማቸው እንደሆነ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በ401 ባለሃያ ጫማ ኮንቴይነሮች 9,303.54 ሜትሪክ ቶን ወጪ ጭነት በራሱ መርከቦች ወደ ቻይና፣ ህንድና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ማጓጓዙ ታውቋል።
በቀይ ባህር በተከሰተው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ትልልቅ የመርከብ ኩባንያዎች ወደ አካባቢው መምጣት መቀነሳቸውን፣ የተወሰኑትም ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውን የድርጅቱ ምንጮች ተናግረዋል።
በተለይ የኢትዮጵያን ቡና ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚያጓጉዙ የመርከብ ድርጅቶች ወደ ሥፍራው ስለማይመጡ፣ ቡና ላኪዎች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ገልጸዋል።
ድርጅቱ በመጋቢት ወር ብቻ 113 ኮንቴይነሮችን ወይም 2.712 ሜትሪክ ቶን ወጪ ጭነት ወደ ህንድና ቻይና ማጓጓዙን፣ አገልግሎቱን በመቀጠልም ሌሎች የመርከብ ድርጅቶች ከሚጠይቁት ክፍያ ሰባት እጥፍ ባነሰ የአገልግሎት ክፍያ እየሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
በቀይ ባህር በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት የመርከብ ኩባንያዎች ወደ ጂቡቲ ወደብ ስለማይመጡ የኮንቴይነር እጥረት በመከሰቱ፣ በርካታ የቡና ኤክስፖርተሮች ቡና ለመላክ መቸገራቸውን በቡና ኤክስፖርት የተሰማሩት አቶ ንጉሤ ለገሠ ለሪፖርተር ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ለኤክስፖርት የተዘጋጀ ቡና መጋዘን ውስጥ ማከማቸታቸውን የገለጹት አቶ ንጉሤ፣ በቀይ ባህር የተከሰተው ችግር ዓለም አቀፍ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ሌላ አማራጭ ወደብ የምትጠቀምበት ዘዴ እንዲፈጠር ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።
ላኪ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በኬንያ የሚገኘውን የሞምባሳ ወደብ እንዲጠቀሙ አማራጭ መቅረቡን፣ ነገር ግን የቡና ኤክስፖርተሮች በትንሹ 38 ሜትሪክ ቶን የሚይዝ ኮንቴይነር እንደሚጠቀሙ አክለው አቶ ንጉሤ ገልጸዋል።
ከናይሮቢ ወደ ሞምባሳ በሚወስደው መንገድ የሚፈቀደው 28 ሜትሪክ ቶን ኮንቴይነር ማጓጓዝ ስለሆነ፣ ይህ አሠራርም ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ፍላጎት ጋር የማይጣጣም መሆኑን አብራርተዋል።
የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከጂቡቲ እስከ ደቡበ አፍሪካ በማጓጓዝ የቡና ምርት ለማስረከብ ዕቅድ መያዙን ጠቅሰው፣ እንዲህ ዓይነቱ ረዥም ሒደት በኤክስፖርተሮች ላይ ተጨማሪ ወጪ የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን አንድ የመርከብ ድርጅት ብቻ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የተናገሩት አቶ ንጉሤ፣ የችግሩንም አሳሳቢነት በመረዳት መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል።
በቀይ ባህር ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ የመርከብ ኩባንያዎች አገልግሎት መስጠት ማቆማቸው፣ በኢትዮጵያ ኤክስፖርተሮች ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን የሎጂስቲክስ ባለሙያው አቶ ግርማ ቡታ ተናግረዋል።
ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ሌሎች ምርቶችን ወደ የተለያዩ አገሮች ለመላክ በመርከብ እንደሚጫንላቸው የሚጠባበቁ ኤክስፖርተሮች፣ መርከቦች መምጣት በማቆማቸው ምክንያት በጂቡቲ ወደብ ምርቶቻቸው እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ሜዲትራኒያን ሺፒንግ ካምፓኒ (ኤሜሲሲ) የሚባል ትልቅ የመርከብ ኩባንያ ጂቡቲ ወደብ በመምጣት፣ የኢትዮጵያን ወጪ ምርቶች እያንቀሳቀሰ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
በመርከብ ኩባንያው አቅም ብቻ የኢትዮጵያን ኤክስፖርት ማንቀሳቀስ እንደማይቻል፣ ኩባንያውም የኮንቴይነር እጥረት እንደሚያጋጥመው ተናግረዋል።
ኩባንያውም በወር አራት ጊዜ ጂቡቲ በመምጣት ወጪ ምርቶችን እንደሚጭን በብትን የሚጫን ቡና ኤክስፖርት ማድረግ እንዳልተቻለ አቶ ግርማ ጠቁመዋል።
የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ በዋናነት የምትጠቀመው የጂቡቲ ወደብ ስለሆነ፣ በርካታ የመርከብ ኩባንያዎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ጂቡቲ መምጣት ማቆማቸውን የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ ጀና ተናግረዋል።
በቀይ ባህር በሚደርሰው ጥቃት ሳቢያ በርካታ የመርከብ ኩባንያዎች እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው መሥራት መቸገራቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ ኤክስፖርተሮች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኤክስፖርተሮች ምርቶቻቸውን ለመላክ ሌላ አማራጭ ወደብ እንዲጠቀሙ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ኤክስፖርተሮች ኮንትራት ከፈጸሙ ድርጅቶች ጋር ውላቸውን እያቋረጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከጂቡቲ ወደ ሞምባሳ የማጓጓዣ ሥርዓትን በመዘርጋት ላይ ቢሆንም፣ ጉዳዩን የቡናና ሻይ ባለሥልጣንን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተነጋገሩበት እንደሆነ አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል።
ምንጭ፦ ሪፖርተር