ክልሉ ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሐብቶች ፈቃድ ሰጠ

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 11 ቢሊየን 490 ሚሊየን 458 ሺህ 249 ብር ላስመዘገቡ ባለሐብቶች ፈቃድ መስጠቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አስታወቀ።

ፈቃዱ የተሰጠው በ26 የግብርና እና በሰባት የኢንዱስትሪ ዘርፎች መሆኑን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡም ለ621 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ18 የግብርና እና በ33 የኢንዱስትሪ ዘርፎች 98 ሚሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሐብቶች ፈቃድ መሰጠቱን አስታውሰው፥ ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ለ460 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ካለፈው ዓመት ጀምሮ እስከ ታኅሣስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በገቡት ውል መሰረት ሥራቸውን ማከናወን ላልቻሉ 20 ባለሐብቶች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን እና 12 ባለሐብቶች ደግሞ ማልማት ያልቻሉትን 2 ሺህ 134 ሔክታር መሬት ተቀናሽ መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የ12 ባለሐብቶችን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ 6 ሺህ 994 ሔክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ መደረጉን አረጋግጠዋል።

በአጠቃላይ በውላቸው መሰረት ማልማት ያልቻሉት 9 ሺህ 182 ሔክታር መሬት ተቀናሽ በማድረግ ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ ተደርጓል ብለዋል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *