
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ ከ260 በላይ የውጭ ባለሀብቶች በተፈቀዱ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ሰራተኞች የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግመዋል።
በዘጠኝ ወራቱ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን ከማሻሻል ፣አዳዲስ ኢንቨስተሮችን ከመሳብና ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር አመርቂ ውጤቶችን መመዝገባቸው ተገልጿል።
የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ለውጭ ባለሀብቶች በተፈቀዱ የወጪ፣ ገቢ፣ ጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ሥራዎች ከ260 በላይ ባለሃብቶች በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳሳዩ ሪፖርቱ አመላክቷል።
ፍላጎት ካሳዩት መካከል የ78ቱ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 40 የውጭ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል።
በሌላ በኩል የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አንጻርም ስኬታማ ስራ መከናወኑም ነው የተገለጸው።
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ብልጫ ያለው ቢሆንም የተሻለ ስራ ማከናወን እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
ከባለድርሻ አካላት ጋርም በተቀናጀ መልኩ ስራን በማከናወን እንዲሁም ለባለሀብቶች ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ፦ ኢዜአ