ከአማራ ክልል ለውጭ ገበያ ከቀረበ ጥሬና የተዋበ ኦፓል እንዲሁም ለብሔራዊ ባንክ ከቀረበ ወርቅ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ እንደተገኘ የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ባለፉት ሥድስት ወራት 10 ሺህ 739 ነጥብ 695 ኪሎ ግራም ጥሬ ኦፓል ወደ ውጭ በመላክ 755 ሺህ 491 ዶላር ለማግኘት ታቅዶ÷ 3 ሺህ 953 ነጥብ 88 ኪሎ ግራም በመላክ 978 ሺህ ዶላር መገኘቱን ቢሮው ገልጿል።
እንዲሁም 1 ሺህ 750 ኪሎ ግራም የተዋበ ኦፓል ወደ ውጭ በመላክ 137 ሺህ 500 ዶላር ለማግኘት ታቅዶ÷ 188 ነጥብ 57 ኪሎ ግራም በመላክ 487 ሺህ 256 ዶላር መገኘቱን ለፋና ዲጂታል አስታውቋል።
በተጨማሪም 65 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማስገባት 5 ሚሊየን 63 ሺህ 775 ነጥብ 57 ዶላር ሊገኝ መቻሉን ገልጿል።
በሌላ በኩል ከሮያሊቲ፣ ከመሬት ኪራይ እና ሌሎች ተዛማጅ የአገልግሎት ክፍያዎች 33 ሚሊየን 171 ሺህ 829 ነጥብ 97 ብር መገኘቱን የገለጸው ቢሮው÷ የዚህ አፈጻጸም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ40 ነጥብ 93 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ጠቅሷል።
1 ሚሊየን 361 ሺህ 74 ቶን ተኪ ምርቶችን በማምረት 102 ሚሊየን 733 ሺህ 19 የአሜሪካ ዶላር ማዳኑን፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ94 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ ማስመዝገቡን አስረድቷል።
ተኪ ምርቶቹም ጅፕሰም፣ ላይም ስቶን፣ ሲሊካ ሳንድ፣ ፑሚስ፣ ድንጋይ ከሰል፣ እምነ በረድ፣ ግራናይት እና ካኦሊን መሆናቸውን አብራርቷል።
ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ