ከንቲባ አዳነች አቤቤ “Liveable and Sustainable Cities: Rejuvenate, Reinvent, Reimagine” በሚል መሪ ቃል በሲንጋፖር እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በጉባኤው በርካታ የአለም ከተሞች መሳተፋቸውንም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ጉባኤው ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና አረንጓዴ በማድረግ፣ የአየር ብክለትን መከላከል እና የፈጣን ለውጥ ማዕከል በማድረግ ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራ ስለማኖር በሰፊው እየመከረ የሚገኝ ሲሆን ልምድ ልውውጥ እና መማማርን ማዕከል ያደረገ ጉባኤ ነው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በC40 አባል ከተሞች አማካይነት በተዘጋጀዉ የፓናል ውይይት ላይ በመሳተፍ በከተማችን ቀጣይነት ያለው እድገት በማረጋገጥ ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች፣ ዕድሎች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ ልምድ ማካፈላቸውንም አስታውቋል።
በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም የተሻለ ከተማን ለመገንባት እየተከናወኑ ባሉ የወንዝ ዳርቻ ስራዎች፣ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች በመገንባት፣ የአረንጓዴ ልማት ኢንሼቲቭን በማከናወን ላይ ስለሚገኙት የኮሪደር ልማት ስራዎች እንዲሁም የሚሰራው ልማት ሁሉ ለሰው ልጆች ተስፋ እና የኑሮ ጫናን የሚያቃልል ይሆኑ ዘንድ ሰው ተኮር ተግባራት በተመለከተ በዝርዝር ማስረዳታቸውም ተመላክቷል።
ከጉባኤው ተሳትፎ ጎን ለጎን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሲንጋፖር ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴስሞንድ ሊ፣ ከተለያዩ ከንቲባዎች፣ ከተማ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም በከተሞች ዙሪያ ከሚሰሩ የድርጅት ተወካዮች ጋር በቀጣይ የትብብር መስኮች ላይ ውይይት ማድረግ መቻላቸውም በመረጃው ተገልጿል።
ምንጭ፦ ኢዜአ