ከአሜሪካው ግዙፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ከሆነው ቦይንግ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
ቦይንግ በቅርቡ የአፍሪካ አህጉር ዋና መሥሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ ለመክፈት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ከቦይንግ ጋር ለረዥም ጊዜ የቆየ ጠንካራ ግንኙነት አለው።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ብዙ ቁጥር ያላቸውን አውሮፕላኖች በማዘዝ በአፍሪካ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን አንስተዋል።
በቅርቡም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ጋር ኢትዮጵያን የአፍሪካ አቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ ሥምምነት መደረጉን ጠቅሰዋል።
ይህንንም ተከትሎ የቦይንግ ኩባንያ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤቱን ለመክፈት ወደ ተግበር መግባቱን ገልጸዋል።
የሚከፈተው ቢሮ የአየር ትራንስፖርትን ብቻ ሳይሆን በኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግም አዲስ አበባን የአፍሪካ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ያፋጥናል ነው ያሉት።
አየር መንገዱ የአውሮፕላን እቃዎችን በማምረት ለቦይንግና ለሌሎች አየር መንገዶች በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳደግ ያስችለዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ለዜጎች የሥራ እድልን በመፍጠር እንዲሁም ዘርፉ ያለውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማፋጠን ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ይህም አጠቃላይ የአቪዬሽን ዘርፉን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አቶ መስፍን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ባሉት 147 በላይ አውሮፕላኖች 136 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።
ምንጭ፦ ኢዜአ