ከቡና ወጪ ምርት 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል

በተያዘው በጀት ዓመት ከቡና ወጪ ምርት 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን የኢትጵዮያ ቡናና ሻይ ባለስጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ÷በተያዘው በጀት ዓመት ከ400 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 2 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰው ባለፉት ሦስት ወራት 115 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በመላክ 520 ሚሊየን ዶላር ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

በሦስት ወራቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በበጀት ዓመቱ ለማግኘት የታቀደውን የ2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ዕቅድ ማሳካት እንደሚቻል አመላካች መሆኑንም ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ  የተያዘውን  ዕቅድ  ለማሳካት  የቡና ምርትና ምርታማነት መጨመር እንዲሁም ጥራት ያለው ቡና ወደ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ጎን ለጎንም የቡና ግብይቱን የሚያሳልጡ አሰራሮችን የመዘርጋትና የገበያ አማራጮችን የማስፋት ሥራዎች በሥፋት እየተከናወኑ  መሆናቸውን ገልፀው በቡና ምርት እሴት የመጨመርና የግብይት ሰንሰለቱን የማሳጠር ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ጀርመን፣  ጃፓን፣  ሳዑዲ አረቢያ፣ ቤልጂየምና አሜሪካ የኢትዮጵያ የውጭ የቡና ገበያ መዳረሻ ሀገራት ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቻይና፣ ደቡብ  ኮሪያና ጆርዳን የኢትዮጵያን ቡና በስፋት የሚገዙ ሀገራት እየሆኑ መምጣታቸው ተመላክቷል።

ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *