ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና የጣልያኑ ፋሬሲን ኩባንያ የአልሙኒየም ፎርም ዎርክ ለማምረት የሚያስችል የ3 ሚሊየን ዩሮ የኮንትራት ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የተፈራረሙት÷ የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የፋሬሲን ፎርም ዎርክ ኩባንያ ዋና ዳይሬክተር ጊያኮሞ ዳላ ፎንታና ናቸው።
ስምምነቱ በግሩፑ ሥር የሚገኘውን የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አንድ ርምጃ ወደፊት እንደሚያራምደው የተገለጸ ሲሆን÷ ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የአልሙኒየም ፎርም ዎርክን በሀገሪቱ በብቸኝነት ለማምረት እንደሚያስችለውም ተመላክቷል።
በዚሁ መሠረት ፋሬሲን ኩባንያ ምርቱን ለማምረት የሚያስችሉ ማሽኖችን፣ ሲኬዲ እና ኤስ ኬዲ ምርቶችን እንደሚያቀርብ መገለጹን የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ መረጃ አመላክቷል።
የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የትብብር እና የማማከር ሥራዎችም በስምምነቱ መሰረት የሚፈጸሙ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን÷ ስምምነቱ ሀገሪቱ በዘርፉ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀር ተጠቁሟል።
የአልሙኒየም ፎርም ዎርክ ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ የግንባታው ዘርፍ እንዲዘምን ከማድረግ ባለፈ÷ የሰው ኃይል ጉልበትን በመቀነስ፣ የግባንባታ ፍጥነትና ጥራት እንዲጨመር ያደርጋል ተብሏል።
በሌላ በኩል ኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና ኤሌክትሪፋይ ኢትዮጵያ ኃ.የተ.የግ.ማ በስትራቴጂካዊ አጋርነት ለቴክኒክ ድጋፍ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አቅርቦት ሥርዓት፣ የባትሪ ኃይል ማከማቻ ስርዓት እና አስፈላጊ አካላት ለማምረት በኢትዮጵያ የማምረቻ ተቋማትን ለማቋቋም የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የኤሌክትሪፋይ ኢትዮጵያ ኃ.የተ.የግ.ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ አበበ (ዶ/ር) መፈራረማቸው ተጠቅሷል።
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ