ኢትዮጵያ በመጪው 10 አመታት ውስጥ 95 በመቶ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በረኦ ሀሠን÷ ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም ረገድ ሰፊ እቅድ ይዛ እየሰራች ነው ብለዋል።
በትራንስፖርት ዘርፍ የኤሌክትሪክ መኪና ምርትን በማፋጠን የነዳጅ ወጪን ለመቀነስና አረንጓዴ ከባቢን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመጪው 10 ዓመታት ከ432 ሺህ እስከ 500 ሺህ የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች 95 በመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ እንደሚሆኑም ነው የገለፁት።
በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ መንግስት ከፍተኛ እገዛና ክትትል እንደሚያደርግ አቶ በረኦ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ወደ 15 የሚጠጉ የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች የኤሌክትሪክ መኪኖችን በመገጣጠም ለአገልግሎት እያቀረቡ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምንጭ፦ ኢዜአ